በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሀኪም ግዛው ሆስፒታል የሲቲ ስካንና ፍሎሮስኮፒ አገልግሎቶች የምርቃት ስነ-ስርዓት ተካሄደ
===============================
መስከረም 27 ቀን 2019 ዓ.ም፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሀኪም ግዛው ሆስፒታል የሲቲ ስካንና ፍሎሮስኮፒ አገልግሎቶችን የምርቃት ስነ-ስርዓት አካሄደ፡፡
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማረ መለሰ፣ የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ገስጥ ጥላሁን፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር የሻለም ገዛህኝ፣ የዩኒቨርሲቲውና የካምፓሱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች፣ የከተማው አመራሮች እንዲሁም የሕብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማረ መለሰ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ የሲቲ ስካንና የፍሎሮስኮፒ አገልግሎቶች የሆስፒታሉ ሕንፃ ግንባታ ሲከናወን አብረው የተገዙ መሆናቸውን ገልጸው፣ ማሽኖቹ በሆስፒታሉ የሚሰጡ የምርመራና የሕክምና አገልግሎቶችን በእጅጉ ለማሻሻል የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ዶ/ር አስማረ አክለውም፣ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ውስን እንደነበር ገልጸው፣ የሀኪም ግዛው ሆስፒታል ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን ወደ ሥራ ማስገባቱ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፣ ሀኪም ግዛው ሆስፒታል በአካባቢው ተመራጭ የጤና ተቋም እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፣ ለዚህም የዩኒቨርሲቲው፣ የካምፓሱና የሆስፒታሉ አመራሮች፣ ሠራተኞችና የጤና ባለሙያዎች ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
የሆስፒታሉን ተመራጭነት የበለጠ ለማሳደግ የማስፋፊያ ግንባታውን በማጠናቀቅና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በመስጠት ረገድ በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነ-ምግባር የታነጹ ባለሙያዎችን ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን ከንቲባው ጠቁመዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ገስጥ ጥላሁን፣ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አስራት ወልደየስ ጤና ሳይንስ ካምፓስ ሀኪም ግዛው ሆስፒታል የደብረ ብርሃንና አካባቢውን ማህበረሰብ የጤና ፍላጎት ለማርካት እያከናወነ ያለውን ሥራ አድንቀዋል።
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የሲቲ ስካን እና የፍሎሮስኮፒ ማሽኖችን ገዝቶ ስራ ማስጀመሩን አስታውቋል፡፡ አዲሶቹ የሲቲ ስካንና ፍሎሮስኮፒ አገልግሎቶች ለሰሜን ሸዋና አጎራባች ዞኖች ነዋሪዎች የምርመራ አገልግሎትን በቅርበት እንዲያገኙ ከማስቻላቸውም በላይ፣ በሪፈራል ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መጓዝ ለሚገደዱ ታካሚዎች የሚደርሰውን አላስፈላጊ እንግልት፣ የጊዜ ብክነትና የገንዘብ ወጪ ለመቀነስ እንደሚያግዙ ተጠቁሟል።