Message

 

 

 

 

“ይህንን ያውቃሉ!”

ትምህርት በተፈጥሮ የተገኘውን አዕምሮን የሚቀርጽ መሳሪያ በመሆኑ ለሥነ-ምግባርም ሆነ ለሌሎች የሰው ልጅ እድገቶች መሰረት ነው፡፡

ትምህርት ባይኖር ኖሮ የሰው ልጆች ውስን የሆነ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ብቻ ይዘው ከቀበሌያቸው፣ ከመንደራቸው ላያልፉ ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለሥነ ምግባር መጐልበትም ሆነ ለአጠቃላይ ሕይወት ስምሪትና እድገት አይረዳቸውም ነበር፡፡

ትምህርት ግን ሁሉንም ነገር ከማወቅ አልፈን እንድንሻሻልበትና ራሳችንን እንድንፈትሽ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ ትምህርት ትልቁ የአዕምሮአችን የልማት መሠረት ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡

 የአዕምሮ ልማት ሲባል እውቀት ወይም ክህሎት ብቻ ሳይሆን አመለካከትንም ይጨምራል፡፡ ሥነ-ምግባርን ስንመለከት ደግሞ ስነ-ምግባር በመሰረቱ ፍልስፍና ነው፡፡ ይህ ፍልስፍና በሰው ልጆች አዕምሮ ውስጥ ሰርጾ የሚገባው ሁሉም የማህበረሰብ አባላት ሲማሩ ነው፡፡ የተማረና በትምህርት የበለፀገ ማህበረሰብ የሥነ-ልቦና ጤንነቱ የተጠበቀ፣ ሌሎችን የማይረብሽና መልካም ሥነ-ምግባር ያለው ትውልድ እንዲፈጠር ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣል፡፡

 ከዚህ ጋር ተያይዞ በሰው ልጆች ዘንድ ሦስት ዓይነት ስብዕናዎች  አሉ፡፡እነርሱም፡-

 1. በመጀመሪያው የስብዕና ዓይነት ውስጥ የሚመደቡ የሰው ልጆች ዓይነት፡-

     ሀ.      ምንም ንቃተ-ሕሊና የሌላቸው፣

     ለ.      ጠቃሚውንና ጐጂውን የማይለዩ፣

     ሐ.      በስሜት ብቻ የሚመሩ ናቸው፡፡

 ከዚህም በተጨማሪ ዕውቀት የላቸውም፣ የሚደርስባቸውን አደጋ አያውቁትም፣ በሌሎች ላይ የሚያደርሱትንም አደጋ አያውቁትም፣ የሌሎችን ስሜትም አይረዱም፡፡

 በጥቅሉ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሥነ ምግባር የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ሥነ ምግባር ሰርጾ ውስጣቸው አልገባም ወይም ገብቶ በተለያዩ ምክንያቶች ጠፍቷል፡፡ ሥነ ምግባር ወደ ውስጣቸው ያልገባው ገና የተወለዱና በማደግ ላይ ያሉ ልጆች ናቸው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሥነ ምግባርም ሰርጾባቸው በተለያዩ ምክንያቶች ለምሳሌ በአዕምሮ ህመም ምክንያት የሥነ ምግባር ደረጃቸው የጠፋባቸው ሰዎችም  ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

 2. ሁለተኛው የሰው ልጆች ስብዕና ሥር ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰዎች ደግሞ ሕጐችን ያውቃሉ፣ የማህበረሰቡን እሴቶችና ያልተጻፉ ሕግጋትን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ስብዕና ያላቸው ሰዎች በሰው ፊት የሚፈጽሙት አንዳች መጥፎ ነገር የለም፡፡ ጠንቃቃ ናቸው፣ ሕግንና ማህበረሰቡን ይፈራሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የሰው ልጆች ስብዕና በዚህ ምድብ ሥር ሊጠቃለል ይችላል፡፡

እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ሥነ-ምግባርን የማይጥሱት ሕጉንና ማህበረሰቡን ስለሚፈሩ ብቻ ነው እንጂ ሥነ-ምግባር ሰርፆባቸው ውስጣቸው ተለውጦ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ስብዕና ያላቸው ሰዎች ማህበረሰቡ ወይም የሕግ አስከባሪዎች በሌሉበት ሁኔታ ሥነ-ምግባርን ከመጣስ በፍጽም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከሙስናና ኢ-ሥነ ምግባር ድርጊቶች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ከዚህ የሰው ልጆች ስብዕና ጋር ተያይዞ የሚታዩ ናቸው፡፡ በተለያዩ መንገዶች የሚያጭበረብሩ ሰዎች የሥነ-ምግባር እውቀት አንሷቸው ሳይሆን ሞራል ወይም የሥነ ምግባር እምነቱ ስላልሰረፀባቸው ነው፡፡

3. ሦስተኛው የሰው ልጆች ስብዕና ሥር የሚጠቀሱ ሰዎች ደግሞ “በሥነምግባር መርህና በሞራል ብቻየሚመሩ ሰዎች ናቸው፡፡ የሰው ልጆች እንዳይጠፋፉ፣ አብረው ተቻችለው እንዲኖሩ ሥነ-ምግባርን ከማወቅና በውስጣቸው ከማስረጽ አልፎ ሌሎችን የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከሥነ ምግባር መርህ ውጭ ወጥተው ሞራሉ የማይፈቅድላቸውን ነገር አያደርጉም፡፡ ከኋይማኖት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአብዛኛው በኃይማኖታዊ መጽሐፍቶች ውስጥ ከሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ በተምሳሌት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰዎችን እናያለን፡፡

እንግዲህ በአሁኑ ወቅት ለአገራችን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጉ ሰዎች ውስጣቸው በሥነ ምግባርና በሞራል የተቀየሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ለማፍራት ደግሞ ማህበረሰባችን ውስጥ የቆዩ በርካታ የግብረ ገብ እሴቶች አሉ፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት እነዚህን እሴቶቻችንን አጐልብተን የመሄድ ሁኔታ በተለይም በከተማው አካባቢ የላላ ይመስላል፡፡ በዚህ ዙሪያ ጠንካራ ሥራ መስራት ይኖርብናል፡፡

ሕጐች በየጊዜው ይወጣሉ፣ ሕግ አስከባሪዎችም አሉን፡፡ ነገር ግን ሕጐቻችን ሞራልን የሚያስከብሩ አይመስሉም፡፡ ምክንያቱም ሕግን የሚያከብሩ ሰዎች ሕግን ስለሚፈሩት ነው እንጂ ሞራል ኖሯቸው ሥነ-ምግባርን መርህ አድርገው ወስደውት ውስጣቸው ተለውጦ አይደለም፡፡ የሥነ ልቦና ትምህርት ሆነ አጠቃላይ ትምህርቱ ይህንን ይቀይራል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለመሆኑ ራሳችንን የትኛው ላይ እንደሆንን እንመዝነው፡፡

 

ምንጭ፡- የፌ/ስ/ም/ፀ/ሙ/ኮሚሽን

ታህሳስ 2009 ዓ/ም መፅሄት

 

“ መልዕክታችንን ሥላነበባችሁልን ምስጋናችን የላቀ ነው”

 

ማሳሰቢያ፡- አስተያየት ካላችሁ በ0116812024 ደውሉልን፡፡

 

 

 

JoomShaper