ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውንተማሪዎች አሰመረቀ

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለ14ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመደበኛ፣ በተከታታይ፣ በክረምትና በማታው መርሐ-ግብሮች በአጠቃላይ ያሰለጠናቸውን 2869 ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል 864 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። በመጀመሪያ ዲግሪ በመደበኛው 928፣ በማታው 459፣ በክረምት ስነ ትምህርት (PGDT) 1306 እና በክረምት 8 ሲሆኑ በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛው 12፣ በማታው 131 እና በክረምት 81 ናቸው። በሶስተኛ ዲግሪ Phd 2 መሆናቸውም ታውቋል።

 

የደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) በቆይታችሁ ብዙ ውጣውረዶችን አልፋችሁ ለቀጣይ ህይወታችሁ ወሳኝ ቀን ላይ በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ ለተመራቂ ተማሪዎቹ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ድህነትን ማምከኛ ብቸኛው ትልቁ መሳሪያ ትምህርት እንደሆነ የገለጹት ፕሬዝደንቱ ዛሬ ኢትዮጵያን ከድህነት የማላቀቅና የበለጸገች አገር የመፍጠር ሀላፊነት ተቀብላችኋል ብለዋል።

ለአገር ልማት በሚደረገው እርብርብ ሁሉ የበኩላችሁን በመወጣት በትምህርት ያገኛችሁትን እውቀትና ችሎታ በተግባር አስመስክሩ ሲሉ ተናግረዋል። እውቀታችሁን ለበጎ ሥራ በማዋልና በጥብቅ ስነ ምግባር በመምራት ብቻ ያስተማራችሁን ማህበረሰብ በማገልገል ውለታውን መልሱ ብለዋል።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ም/የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አብርሐም ኃይለአምላክ ሀገራችን ኢትዮጵያ ደሀ ብትሆንም በበርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ብትፈተንም በትምህርት ሂደቱ ላይ እየሰራች ያለችውን በርካታ ስራዎች አጠናክራ ቀጥላለች ብለዋል። ሀገራችን በትምህርት ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት በእውቀትና በክህሎት የበለጸገ የሰው ሀይል ለሀገራዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ነው ብለዋል። እናንተም የዚህ ሰፊ ኢንቨስትመንት ውጤት በመሆናችሁ በሰለጠናችሁበት የሙያ መስክ ስራን ከቀጣሪዎች በመፈለግ ብቻ ሳይሆን የሥራ ፈጣሪ በመሆን ለሀገራችሁ ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት የበኩላችሁን በመወጣት ታሪክ ሰሪ እንድትሆኑ ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰሩ አክለውም ስራን በወሬ ሳይሆን በተግባር የምታረጋግጡ፣ ህዝባችሁንና ሀገራችሁን በቅንነት፣ በታማኝነትና በታታሪነት የምታገለግሉ በሥራ ዘመናችሁ ሁሉ የመፍትሄ አመንጪ እንጂ ችግር ፈጣሪ እንዳትሆኑ ሲሉ ተናግረዋል።

ለቀጣይ የህይወት ምእራፍ ጅማሮ ከወዲሁ ዝግጅት በመጀመርም እስከአሁን ያካበታችሁትን እውቀት፣ ክህሎትና ጥበብን ሰንቃችሁ በገጠመኞቻችሁ እየተፈተናችሁ ህዝባችሁን ከወዲሁ ለማገልገል መዘጋጀት አለባችሁ ብለዋል።

3.94 አጠቃላይ ውጤት በማምጣት ከህግ ትምህርት ክፍል ተማሪ ገሊላ ወጋየሁ የወርቅና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ-ግብሮች ከ24 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል።

JoomShaper