የደብረ
ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአይሲቲ ስራ አስፈጻሚ የሲስተም አድምንስትሬሽን ቡድን መሪ ዳዊት አባተ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በ2017
ዓ/ም የትምህርት ዘመን የትምህርት አሰጣጥ ስርአቱን ዲጂታል ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ለመግባት
የሚያችሉ የአቅም መገንቢያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳዊት በዛሬው እለት ከ118 በላይ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ
ኮሌጅ መምህራን ቴክኖሎጂውንና አጠቃቀሙን በተመለከተ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ አክለውም የተዘጋጀው ፕላት ፎርም የወረቀት
ስርአትን በተወሰነ ደረጃ የሚያስቀርና የፈተና ስርአቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የሚያደርግ በመሆኑ መምህራንና ተማሪዎችን አንድ ለአንድ
በማገናኘት ውጤታማ የትምህርት ሁኔታን ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ስልጠናው ቀጣይነት ኖሮት በሁሉም ኮሌጆች ተግባራዊ
እንደሚሆን አቶ ዳዊት አባተ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን ያስተባበሩት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን መስፍን ወልደአረጋይ (ዶ/ር) የአሁኑ ስልጠና የመማር ማስተማር ሂደቱ ቴክኖሎጂን የተከተለ እንዲሆን በማሰብ የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አክለውም መማር ማስተማር ስነ ዘዴውን በዲጂታል አማራጭ መስጠት ያስፈለገው ቀለል ባለና በተቀላጠፈ መንገድ ኮርሱን ለመስጠትና መምህሩን ከተማሪው ጋር በቀጥታ ለማገናኘት ስለሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ፕላት ፎርም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተግባራዊ እየተደረገ በመሆኑ ካሉት የዲጂታል አማራጮች ለዩኒቨርሲቲያችን ተማራጭ የሆነውን መርጠን በመማር ማስተማር ሂደትና በፈተና ወቅት ተግባር ላይ እንዲውል ስናስብ ሲስተሙ ጊዜ ቆጣቢና ብዙ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ማሳተፍ በመቻሉ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አቶ ደጀኔ ሸዋቀና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የሒሳብ ትምህርት ክፍል መምህር የዛሬውን የኦንላይን ሲስተም የክፍል ውስጥ የማስተማር ስነ ዘዴ ስልጠና ስንሰጥ አሁን ያለንበት የአለም ነባራዊ ሁኔታ ቴክኖሎጂውን የግድ ለመጠቀም ስለሚያስገድደን ነው ብለዋል፡፡ መምህራንም የራሳቸውን ዝግጅት የሚያደርጉበት፣ ከአዳዲስ ጉዳዮች ጋር የሚተዋወቁበት፣ ሰፊ እውቀት የሚገበዩበትና ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምድ የሚያዳብሩበት በመሆኑ ከኢንተርኔት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ከሚታዩ ችግሮች በስተቀር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡