ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡

News news
2025-09-25 08:22:05

ደብረ ብርሃን  ዩኒቨርሲቲ መስከረም 15/2018 ዓ.ም፡፡ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከሰሜን ሸዋ ከፍተኛ ፍ/ቤት ጋር የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡

የመክፈቻ ንግግሩን ያደረጉት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአለማቀፍ ግንኙነት ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ቤተል ገረመው (ዶ/ር) እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከከፍተኛው ፍ/ቤት ጋር  በጋራ ሊሰሩባቸው ባቀዱት የስራ ዘርፎች ላይ የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ለማካሄድ የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ ዲን አቶ ሆነልኝ ሃይሉ እንደገለፁት ቀደም ብሎ ከከፍተኛ ፍ/ቤት ጋር በጋራ በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን በመናገር የ5ኛ አመት ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ተገቢውን  የህግ ክህሎት እንዲያገኙ በማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ አክውም ዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች የሁለተኛ ድግሪ ትምህርት ተጠቃሚ ሆነዋል እንዲሁም በተጋባዥ መ/ርነት ተግባር ተኮር ትምህርት ለተማሪዎች እንዲሰጡ በማድረግ ፣በህግ ትምህርት ቤት የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች  ላይ ገምጋሚና ተመራማሪ በመሆን ፣ለዳኞች ፣ለተሿሚዎች ፣የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት በጋራ እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በመቀጠልም በአዲሱ ሰነድ እቅድ ከ5ኛ አመት በታች ላሉ የህግ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ (ኢንተርን ሺፕ) እንዲያገኙ የከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች እና መምህራን የምርምር ስራን በጋራ ለማድረግ፣ለከፍተኛው ፍ/ቤት ዳኞችና  በስሩ ላሉ ዳኞች ስልጠናዎችን ለመስጠት ፣የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ  (ዶ/ር) ምስጋና በማቅረብ እንደ ዩኒቨርሲቲ  ቅድሚያ ከምንሰጣቸው አጋሮቻችን አንዱ  ከፍተኛው ፍ/ቤት ነው በማለት  የተለያዩ ስራዎችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም  ተማሪዎችን  የእውቀትና  የክህሎት  ባለቤት ማድረግ   በጋራ አካባቢን ብሎም አገርን በመገንባት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ 

የሰሜን ሸዋ ዞን የከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች አስተዳደር ንኡስ ፅቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ደጀኔ እንደገለፁት የህግ ተማሪዎች በፍትህ ተቋማት ተግባር ተኮር እውቀት የሚያገኙባቸው መሆን እንዳለባቸው በመናገር ለማህበረሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እቅዶችን በማቀድ በጋራ እንሰራለን በማለት ገልፀዋል፡፡    

የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዮሃንስ ወንድሙ የምንሰራቸው ስራዎች የማህበረሰቡን አገልግሎት  ለመጨመር፣ በተግባር ወደ መሬት ወርደው ግልጋሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ሰነዱን ለመፈራረም ስለበቃን እጅግ ደስተኛ ነኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በእለቱም የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች እና የከፍተኛው ፍ/ቤት ዳኞች በተገኙበት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት  አስማረ መለሰ (ዶር) እና የከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶዮሃንስ ወንድሙ የሁለትዮሽ የጋራ ሰነድ ፊርማ ተፈራርመው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

555673896_826281269730109_495725953480617500_n-(1)-488772.jpg 553323402_826281396396763_3003030171189654929_n-754134.jpg 555048654_826281353063434_5388421242021888082_n-594697.jpg