የመክፈቻ ንግግሩን ያደረጉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ(ዶ/ር) እንደተናገሩት በአሉን ልዩ የሚያደርገው ተራ የቀን መቁጠሪያ ሳይሆን የሰው ልጅ ግማሽ አካል በሆኑት ሴቶች በታሪክና በእውቀት ጉዞ ውስጥ የሚያሳዩትን ተፅእኖ ፈጣሪነት የሚወደስበት የክብር መድረክ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡አክለውም ሴት ምሁራን በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ሚና ‹‹ተሳትፎ››ከሚለው ቃል በላይ እንደሆነ ተናግረው ሴቶች በትምህርት በሚያበረክቱት ሳይንሳዊ ምርምር የቴክኖሎጂ ፈጠራና በሚሰጡት የማህበረሰብ አገልግሎት የተቋሙን ህልውና በማረጋገጥ የላቀ አስተዋፅኦ መሆኑ እንዲሁም መጪውን ትውልድ በእውቀት ብቻ ሳይሆን በስነ--ምግባር በመቅረፅ የሚጫወቱት ሚና ለሃገራዊ ህልውናችን ወሳኝና የማይተካ መሆኑን ገልፀዋል፡፡በተጨማሪም እንደ ዩኒቨርሲቲ አመራር ሴቶችን በውሳኔ ሰጭ ቦታዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጎለብቱ ፣ምቹ የስራ አካባቢ እንዲፈጠርላቸው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው ፕሮግራሙን ከፍተዋል፡፡
ክብርት አየለች እሸቴ በኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት እንደገለፁት የዩኒቨርሲቲ ሴት ምሁራን በማስተማሩ ብቻ ሳይሆን ትውልድን በመቅረፅ ጉልህ ሚና ያላቸው፣መሪዎችና መካሪዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም ሴቶች በትምህርት በፖለቲካ ፣በሳይንስ፣በምርምር፣በኢኮኖሚክስ እና በሰላም ግንባታ ወደርየለሽ ሚናን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በእለቱም በበአሉ የተገኙ እንግዶች፣የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን፣ሴት የአስተዳደር ሰራተኞች በአሉን በማስመልከት በደብረብርሃን ከተማ በአፄ ዘርአያቆብ ክፍለ ከተማ ስራና ስልጠና ፅ/ቤት 3 ሴቶች በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው የከፈቱትን ጋርመንት፣ እንዲሁም 4 ሴቶች ተደራጅተው የከፈቱትን እታገኘሁና ኑኑ ጓደኞቻቸው የሴቶች ዊግ ማምረት ህብረት ስራ ማህበርን እና ሰላም ጮራ ቀበሌ አካባቢ የሚገኘውን የማለፊያ ምንጭ የልማት ህብረት ቡድንን ጉብኝት በማድረግ ምክርና አድናቆታቸውን ለግሰዋል፡፡
በፕሮግራሙም የደብረብርሃን ዩኚቨርሲቲ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አዲስ አስፋወሰን ለዩኒቨርሲቲው ሴት ምሁራን የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ ፣የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን አስተዋፅኦ ምንድነው? የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን የሚያጋጥማቸው ፈተናዎች፣ ሴት ምሁራን በሃገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባ ሚናዎች ወ.ዘ.ተ በሚሉ ርእሶች ዙሪያ የመወያያ ሰነድ አቅርበዋል፡፡
በመቀጠል የደብረብርሃን ሪጂኦ ፖሊታን ከተማ አስተዳደር የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ክብርት በለጥሽ ግርማ የወቅቱ የስነ-- ህዝብ ሁኔታ የሴቶችን ቁጥር በተመለከተ ፣የታሪክ ምእራፎች ዳሰሳ በንጉሳዊ ዘመን ፣አርበኝነትና የሴቶች ሚና በንጉሳዊ ዘመን ፣የሴቶች የትጥቅ ትግል ከደጀን እስከ ግንባርና ወ.ዘ.ተ በሚሉ ርእሶች የመወያያ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ በቀረቡት ሰነዶች ዙሪያ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ውይይቱን የመሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ (ዶ/ር) እና ተጋበዥ እንግዶች ናቸው፡፡በመጨረሻም የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተዘምሮ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡