በአህሪ እና በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በጋራ በሚሰሩ ስራዎች አፈፃፀም ላይ የምክክር መድረክ ተካሄደ
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና በአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት /AHRI/ መካከል በትምህርት፣ በምርምር እና በአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ዙሪያ ሚያዚያ 23
ቀን 2018 ዓ.ም በአስራት ወልደየስ ጤና ሳይንስ ካምፓስ የስብሰባ አዳራሽ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
በምክክር መድረኩ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ
ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ሲሳይ ሙላቴ (ዶ/ር)፣ የአስራት
ወልደየስ ጤና ሳይንስ ካምፓስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ ክፍለዮሐንስ፣ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ተቋምን ወክለው የተገኙ ልዑካን ቡድን እንዲሁም
የካምፓሱ ሲኒየር ተመራማሪዎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡
በመድረኩ ለውይይት መነሻ የሆነ ሪፖርት በአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ በዶ/ር
ብርሃኑ ስዩም የቀረቡ ሲሆን በሁለቱ ተቋማት አማካኝነት በትምህርት እድል፣ በምርምር፣ በአቅም
ግንባታ ስልጠናዎች እና በሌሎች የማማከር አገልግሎት ስራዎች ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን
በዝርዝር ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ
ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ሲሳይ ሙላቴ (ዶ/ር) እንዳሉት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ላለፉት ዓመታት በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አንስተው
እስካሁን ከተሄደበት ጉዞ በተሻለ መልኩ በጋራ መሰራት ያለባቸው የትብብር ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡ ሁለቱም ተቋማት
በጋራ የሚሰሩ ምርምሮችን በጋራ ፋይናንስ አድርገው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ሲሳይ አክለውም በተመረጡ እና
ዲስፕሊን ቤዝድ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በስፋት አጫጭር ስልጠናዎች በጋራ ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአስራት ወልደየስ ጤና
ሳይንስ ካምፓስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ ክፍለዮሐንስ በበኩላቸው አህሪ እና ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በጋራ የሰሯቸው
ስራዎች እንደ ሀገር ከፍተኛ ውጤቶችን ያመጡ እና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆን ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡ የሀገር በቀል
እውቀቶችንና በአካባቢያችን ያሉ ጸጋዎችን ለመጠቀም በጤና ሳይንስ ካምፓስ ደረጃ የባህላዊ ህክምና ትምህርት ፕሮግራም መከፈት
እንደሚኖርበት ገልጸው ይህ ደግሞ አህሪ ካሉ ምሁራን ጋር በትብብር የሚካሄድና የእርስ በርስ ግንኙነታችንን የበለጠ የሚያጠናክር
ነው ብለዋል፡፡
የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ልዑካን ቡድን በመወከል ዶ/ር አክሊሉ አለሙ ከመድረኩ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት የተመራማሪዎች ቡድን ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት የተካሄደው ውይይት ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር የእርስ በርስ ግንኙነትን የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡