2026-05-04 03:59:34
በፕሮግራሙ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ ገሰሰው ረታ(ዶ/ር) እንደተናገሩት እንደኮሌጅ በፊዚክስ ትምህርት ክፍል እነዚህን የትምህርት ፕሮግራሞች ለመክፈት እንደታሰበና በተለይ በ2ኛ ድግሪ ፕሮግራም የሚከፈተው Astronomy and Astro Physics በሀገር ደረጃ የተቋቋሙ በስነ-ፈለግና ስነ- ከዋከብት ዙሪያ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እየሰራው ያለውን ስራ በምርምርና በቴክኖሎጂ ለመደገፍም ጭምር ያግዛል ብለዋል፡፡ አክለውም ሁለቱም የትምህርት ፕሮግራሞች ከዩኒቨርሲቲ አልፈው ለማህበረሰብና ለሀገር ትልቅ ጥቅም ያላቸው መሆናቸው በጥናት እንደተረጋገጠ ጭምር ተናግረዋል፡፡
በመድረኩም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ምንባለ ጋሹ(ዶ/ር) እንደገለፁት የዚህ ፕሮግራም ዋና አላማ በኮሌጁ ሁለት የትምህርት ፕሮግራሞችን ለመክፈትና በነዚህ ፕሮግራሞች ዙሪያ ሀሳብና አስተያየት ከውስጥና ከውጭ ገምጋሚዎች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት በመውሰድ ሰነዱን የበለጠ ለማዳበር እንደታሰበ ተናግረዋል፡፡ አክለውም እነዚህ ፕሮግራሞች ከምህንድስና ኮሌጅ ጋር በጋራ አብሮ ለመስራት እንደታሰበና በጋራ መሰራቱም ጥሩና ውጤታማ ስራ ለመስራት እንደሚያግዝም ጨምረው አብራርተዋል፡፡
በመድረኩም ሁለት የትምህርት ፕሮግራም ሰነዶች እንደቀረቡና የቀረቡትም ሰነዶች-Phd in Nuclear Sciince and Engineering በአወቀ ታደሰ (ዶ/ር) እና - M,sc Astronomy and Astro Physics በገሰሰው ረታ(ዶ/ር) እንደቀረቡና በቀረቡት ሰነዶች ዙሪያ ሀሳብና አስተያየት ከውስጥና ከውጭ በመጡ ገምጋሚዎች ሲሰጥ ለማየት ተችሏል፡፡
በመጨረሻም የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ምንባለ ጋሹ(ዶ/ር) እንዳሉት ጊዚያቸውን መሰዋእት አድረገው ይህንን የካሪክለም ግምገማ ለመሳተፍ ለመጡ የውስጥና የውጭ ገምጋሚዎች እንዲሁም ለተሳታፊዎች በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋና በማቅረብ የተሰጡትን ሀሳብና አስተያየቶች ለሰነዱ እንደግብዓት በመጠቀም የበለጠ ለማዳበር ያስችላል ብለዋል፡፡