news
2026-05-04 03:21:14
የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግሩን ያደረጉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ገበያው ስጦታው (ዶ/ር)እንዳሉት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የምርምር ጥናት አቅራቢዎች፣ከተለያዩ ሴክተር መስራያ ቤቶች የመጡና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶችን ለ2ኛው አመታዊ የምርምር ኮንፈረንስ ላይ በመገኘታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ቀጥለውም ፕሮግራሙ ምሁራንና ባለ ድርሻ አካላት በማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ እንዲሁም ለችግሮቹ አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦችን እንዲያመነጩ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን በመናገር የዲጂታል ማህበረሰብ፣ ቴክኖሎጂ፣ ትምህርት እና የቀደምት ዕውቀት (Indigenous knowledge)፣ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ እና ከተማነትን በመሳሰሉት ዘርፎች የሚዳሰሱበት በተለይም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ለውጦች የሚታዩበት በመሆኑ፣ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመወጣት አዳዲስ የአስተሳሰብ አድማሶችን ለማስፋት ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ላይ በመወያየትና በጋራ በመስራት ለችግሩ መፍትሄ መፈለግ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የመክፈቻ ንግግሩን ያደረጉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ል ፕሬዚዳንት ሲሳይ ሙላቴ (ዶ/ር) ፕሮግራሙን አስመልክተው እንደተናገሩት ኮሌጆች ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ሃሳቦችን ማፍለቅ ከከፍተኛ ተቋም የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የማህበረሰቡ ባህል፣ታሪክና ቋንቋ በአለም አቀፍ ደረጃ የለማና የዘመነ እንዲሁም ተወዳዳሪ እንዲሆን እንደ ከፍተኛ ተቋም ደግሞ በቀጣይነት ምን መሰራት እንዳለበት የሚያመላክት እውቀት የሚያስጨብጥ የውይይት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም በፕሮግራሙ ምሁራንና ተመራማሪዎች በወቅታዊ ማህበራዊና ቴክኖሎጂያዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ ለማድረግ የጥናት ውጤቶቻቸውን እና ተሞክሮዎቻቸውን የሚያጋሩበት ወሳኝ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። በንግግራቸውም በጉባኤው የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች እና አመለካከቶች ለማህበራዊ ሳይንስ እና ስነሰብ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸውም ጭምር በመናገር የአካዳሚክ ማህበረሰቡ ከማስተማር እና ምርምር ባለፈ ለማህበራዊ ለውጥ (Social Transformation) ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡በተጨማሪም አዳዲስ ሃሳቦችና እውቀቶች ፖሊሲን ለመቅረጽ፣ ፈጠራን ለማነቃቃት እና ማህበረሰብን ለማብቃት መዋል እንዳለባቸው በመግለፅ ጉባኤው እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ አዘጋጅ ኮሚቴዎችና አጋር አካላት ምስጋና በማቅረብ ፕሮግራሙን ከፍተዋል፡፡
በፕሮግራሙም ቁልፍ ንግግር ያደረጉት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፎክሎር ትምህርት ክፍል እና የመላክ አርትስ ወርክ ዳይሬክተር አንዷለም አባተ(ዶ/ር )(የአፀደ ልጅ)እንዳሉት በፕሮግራሙ በመገኘታቸው ምስጋና በማቅረብ በአሁኑ ወቅት አለም በፈጣን የለውጥ ግስጋሴ ውስጥ እንደምትገኝ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ምጥቀቱ ባህልን ፣ማህበራዊ ትስስርን አካባቢን በአስደንጋጭ ሁኔታ እየቀየረ በመሆኑ በለውጥ ሂደት ውስጥ ደግሞ የማይታለፍ ፈታኝ ጥያቄ በመኖሩ ቀጣዩ ትውልድ የሚወርሰው አለም ምን አይነት መሆን ይኖርበታል?የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ማህበረሰቡን ፣ባህልንና አካባቢን እንደገና መቅረፅ ግድ መሆኑን ተናግረው ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ ተፈጥሮና የሰው ልጅን አስታርቀው ያኖሩ አይተኬ የሆኑ ድንቅ ባህልና እሴቶች ያሏት ህዝቦች ናቸው እነዚህን እሴቶች ፣ወጎችና ልማዶች ለዚህ ዘመን ተስማሚ በሆነ አውድ ውስጥ ተሸምነው ታድሰው ጥቅም ላይ ከዋሉ በረከታቸው ከሀገር አልፎ ለአለም ተራፊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡በመልዕክታቸውም ዘላቂነት የአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ ሳይሆን የእለት ተእለት የአኗኗር ዘይቤ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የፕሮግራሙ አስተባባሪ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ገበያው ስጦታው (ዶ/ር) የፕሮግራሙን ዋና አላማ አስመልክተው እንደገለፁት ከማህበራዊ ስነ-ሰብ ኮሌጅ ጋር በጋራ በመሆን ሰውና ማህበራዊ ጉድኝቱን ለማስተሳሰር ሁለቱን ሳይንሶች አንድላይ በማምጣት፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ መቀያየር የድሮውን አስተሳሰቦች አሁን ካለው አስተሳሰብ እንዴት ማገናኘት እንደሚቻል ማህበረሰቡ የራሱ የሆነ ትውፊት ቢኖረውም የአውሮፓውያንን ባህል ተፅእኖ እያደረገ በመምጣቱ ትውልዱ ቀጣይነት ባለው መልኩ የራሱን ባህልና ወግ ጠንቅቆ በማወቅ ባህሉን የቴክኖሎጂ መጠቀሚያ እንጂ ቴክኖሎጂው ባህሉ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፊያ እንዳይሆን ለማድረግ በተጨማሪም አጋር አካላትን ለማምጣት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡በመቀጠልም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የምርምር ፅሁፍ አቅራቢ ምሁራን፣ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የመጡ ባለሙያዎች፣ተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት በፕሮግራሙ እንደተገኙ ገልፀዋል፡፡
በእለቱም ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ምሁራን 8 የምርምር ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡በመቀጠልም ጥናትቱን ላቀረቡ ምሁራንና ቁልፍ ንግግር ላደረጉት አንዷለም አባተ (ዶ/ር) ሰርተፍኬት ተሰጥቷል፡፡
የመዝጊያ ንግግሩን ያደረጉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምር ህትመት ስነ-ምግባርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዘመኑ ቢረስ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመድረኩ ዓላማ ዩኒቨርሲቲው እንደ ተግባራዊ (Applied University) በምርም ዘርፍ የማህበረሰቡን ችግር ለመቅረፍና በላቀ ደረጃ ለመወጣት ተልዕኮ የተጣለበት መሆኑን ተናግረው ለፕሮግራሙ መሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እንዲሁም ከአካባቢ እና ከኅብረተሰብ ጋር በተያያዙ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺ ጥናቶችን ላቀረቡ ምሁራን ምስጋና በማቅረብ ፕሮግራሙን ዘግተዋል፡፡
Attachments Gallery
5 images