ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሄደ

News news
2026-08-12 05:30:48

ደብረ ብርሃን (ነሐሴ 05 ቀን 2018 .) — ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣ የካምፓስ ማህበረሰብ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት የተካሄደውን አህጉራዊ እና ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ አካል የሆነ ተቋማዊ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በዋናው ግቢ በይፋ አካሂዷል።

በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ (/) ተቋሙ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለሥነ-ምህዳር መረጋገጥ የሚሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት አብራርተዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ዩኒቨርሲቲው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን በተደራጀና በተቀናጀ አሰራር በአንኮበር እና በሸዋሮቢት የምርምር ማዕከላት ለበርካታ ዓመታት ሲተገብር መቆየቱን አስታውሰው፤ ባለፈው ዓመት በተነደፈው ስልታዊ ዕቅድ መሠረት ደግሞ በመሐል ሜዳ ካምፓስ የችግኝ ተከላና ተከታታይ የእንክብካቤ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ዶክተር አስማረ አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት፣ በቀጣይም ተቋሙ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት (Integrated Watershed Management) አቀራረብን በመከተል የላቀ አካባቢያዊና አካዳሚያዊ ውጤት ለማስመዝገብ ይሰራል። ይህ ተቋማዊ እንቅስቃሴ ለግብርና ኮሌጅ የመማር-ማስተማር፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ምቹ የተፈጥሮ ላቦራቶሪ ከመፍጠሩ ባሻገር፣ ለሌሎች ሀገራዊ ተቋማትም በምሳሌነት የሚጠቀስ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የመርሃ-ግብሩ አስተባባሪ የሆኑት የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መቅደስ ጌራወርቅ (ረዳት ፕሮፌሰር) ደብረ ብርሃን ከተማ ፈጣን የኢንዱስትሪ ማዕከል እየሆነች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ስነ-ምህዳራዊ ጫናዎችንና የአካባቢ ብክለትን ለመቋቋም ከተማ አቀፍ ተቋማዊ ቅንጅትና የተክሎች እንክብካቤ ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል። በዚህም መሠረት ዩኒቨርሲቲው በመሐል ሜዳ፣ በአስራት ወልደየስ ካምፓሶች እና በአንኮበር ቦታኒካል ጋርደን የታቀዱ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በስኬት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር መቅደስ አክለውም፣ ቀደም ሲል ለተከላ የሚሆኑ ችግኞች ከውጭ አካላት በግዥ የሚቀርቡ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ ግን ተቋማዊ ራስ-ችሎታን በመገንባት በምርምር፣ ህትመትና ስርጭት ዳይሬክቶሬት 3 ዓይነት እንዲሁም በግቢ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት 2 ዓይነት በጠቅላላው 5 የስነ-ምህዳር ተስማሚ የችግኝ ዝርያዎች በከፍተኛ መጠን በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢና በመሐል ሜዳ ችግኝ ጣቢያዎች እንዲዘጋጁ መደረጉን አብራርተዋል።

በዚሁ ዕለት በተካሄደው መርሃ-ግብርም የስነ-ምህዳር ጥገናንና ውበትን ታሳቢ ያደረጉ የሀበሻ ጽድ፣ የፈረንጅ ጽድ፣ የፈረንጅ ግራር፣ ግራቪሊያ እና ፓይንስፑላ የተሰኙ የችግኝ ዝርያዎች በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ተተክለዋል።