ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ130ኛውን የአድዋ ድል በዓል በድምቀት አከበረ

News news
2026-03-10 04:10:09

የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት አርማ እና የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት መሆኑን በሚዘክር በዚህ መርሃ ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ አባት አርበኞች፣ ምሁራን፣ ሰራተኞችና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

‎‎​የበዓሉን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሳይ ሙላቴ (/) እንደገለጹት፤ አድዋ ኢትዮጵያውያን መሪና ህዝብ፣ ወንድና ሴት ሳይለዩ በአንድነት ቆመው ለአለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ብርሃን የፈነጠቁበት ታሪካዊ ክስተት ነው።

‎‎ዶክተር ሲሳይ "አድዋ የጀግንነት ሀውልት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያዊያን የጥበብና የስትራቴጂ ውጤት ነው" በማለት ገልጸው፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ (ብርሃነ ዘኢትዮጵያ) ህዝብን ከመሪው በማቀናጀት የማይቻል የሚመስለውን ድል በተግባር ማሳየታቸውን አስገንዝበዋል።

‎‎አክለውም የዛሬው ትውልድ ከአባቶቹ ጀግንነት ባለፈ በወቅቱ የነበረውን የጥበብና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መማር እንዳለበትና በምርምር የታገዘ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማምጣት አገራችንን ማሳደግ እንዳለብን አሳስበዋል።

‎‎​የዩኒቨርሲቲው የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ የባህል፣ የታሪክና የቋንቋ ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ዘመነወርቅ ዮሐንስ (/) በበኩላቸው፤ በዓሉ በመሪ ቃሉ መከበሩ ለታሪካዊው ድል የሚገባ እውቅና መሆኑን ገልጸዋል።

‎‎ዳይሬክተሩ አክለውም "አድዋ ዘመን ተሻጋሪ ቅርስና ለትውልድ የሚቀጥል አሻራ ነው" በማለት፤ ድሉ ባለፈ ታሪክ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ለዛሬውም ሆነ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚተርፍ "አሻራ ተረካቢ ውርስና ቅርስ" መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

‎‎ማዕከሉ በዓሉን ሲያዘጋጅ ታሪኩ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ህያው ሆኖ እንዲጠበቅና ወጣቱ የአባቶቹን የጽናት ታሪክ ተረክቦ ለሀገሩ የሚጠበቅበትን አሻራ እንዲያኖር ለማስቻል መሆኑንም አስገንዝበዋል።

‎‎​ከዚህ የጥበብና የስትራቴጂ ዳራ በመነሳት፣ "የአድዋና የፓን አፍሪካዊነት እሴቶች ለእውነተኛ የአፍሪካ ነፃነት ማረጋገጫ መንገዶች" በሚል ርዕስ በዶ/ አያሌው ዘለቀ ጥናታዊ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን፤ በተነሳው ሃሳብ ላይም ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

‎‎/ አያሌው በጥናታቸው የአድዋ ድል ለፓን አፍሪካዊነት እንቅስቃሴ መንፈሳዊ ስንቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኩዋሜ ንክሩማህን ራዕይና የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን አህጉራዊ ጥረት ከአድዋ ድል ጋር በማያያዝ አብራርተዋል።

‎‎​በቀረበው ጥናትና በተደረገው ውይይትም፤ የአፍሪካ የትምህርት ስርአት መፈተሽ፣ ድሉ በትምህርት ስርአቱ መካተቱን ማረጋገጥና ኢትዮጵያ በመሪነት ሚናዋ እንድትቀጥል ማስቻል የሚሉ ጠንካራ ምክረ-ሀሳቦች ተንፀባርቀዋል።

‎‎ጥናቱ በመደምደሚያው አፍሪካ ዛሬም ድረስ በኒዮ-ሊበራሊዝም (አዲስ ቅኝ አገዛዝ) ስር መሆኗን በመረዳት፣ ድሉን እንደ ጽንሰ-ሀሳብና ፍልስፍና በመውሰድ ለጋራ አህጉራዊ ብልጽግና መጠቀም እንደሚገባ አመላክቷል።

‎‎"​ወጣቱ ከአድዋ አባቶቹ ብዙ የሚማረው ነገር ይኖራል" የሚለው የዚህ ትውልድ ዋነኛ የቤት ስራ መሆኑ የተመላከተበት ይህ በዓል፤ በልዩ ልዩ ስነ-ግጥሞች፣ የስእል ስራዎች፣ ዝክረ አድዋ ተውኔትና ታሪካዊ ትርኢቶች ታጅቦ በድምቀት ተጠናቋል።