የ2018 የትምህርት ዘመን 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን በልዩ ድጋፍ ለማብቃት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄደ።

News news
2025-09-25 08:16:42

ደብረ ብርሃን ዩኒቨረሲቲ የ2018 የትምህርት ዘመን 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን በልዩድጋፍ  ለማብ ቃት በዛሬው እለት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር አካሂዷል። በመርሀ ግብሩ የደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማረ መለሠ (ዶ/ር))፣ የሰ/ሸ/ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ፣ የሰ/ሸ/ዞን ትም/መምሪያ ኅላፊ አቶ ፀጋዬ እንግዳወርቅና የደ/ብርሃን ከተማ ትም/መምሪያ ኅላፊ ወ/ሮ መቅደስ ብዙነህ የተገኙ ሲሆን በዞኑ አስተዳደር፣ በዞኑ ትም/መምሪያ፣ በደ/ብርሃን ከተማ ትም/መምሪያና በደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መካከል  የመግባቢያ ፊርማ ስነስርአት ተከናውኗል።

‎የደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስማረ መለሠ ከባለፈው አመት ልምድ በመነሳት በ2018 ዓ/ም ጊዜ ሳናጠፋ የተሻለ የተማሪ ቁጥር ለመቀበል ዝግጅት ጨርሰን ተማሪዎችን እየጠበቅን ነው ብለዋል። ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ተማሪ ማብቃት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ በመግለጽም በዘንድሮው የማጠናከሪያ ትምህርት ፕሮግራም ተማሪዎችን ከማሳለፍ ባሻገር በላቀ ውጤት 100 ፐርሰንት የማሳለፍ ምጣኔን ይዘን ነው የምንሰራው ብለዋል።

‎የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እንዳሉት በባለፈው አመት ያጋጠሙ ችግሮች እንዳይደገሙ በጥራት ይሰራል።  በተጨማሪም ከአሁን ጀምሮ በቅርበት ትም/ቤቶችን በመደገፍ በተለይ በዘንድሮው አመት ውጤታማ ስራ ይሰራል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ። 

‎ስራው በጥብቅ ዲሲፒሊን እንዲመራም ለዩኒቨርሲቲው የትምህርት ባለሙያዎች፣ ለዞኑ አስተዳደር፣ ለዞኑ ትም/መምሪያና ለደ/ብርሃን ከተማ ትም/መምሪያ አስገንዝበዋል። 

‎የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር መቅደስ ጌራወርቅ በባለፈው አመት እንደክልል ተነሳሽነቱን ወስደን ከዞኑ ትም/መምሪያና ከደ/ብርሃን ከተማ ትም/መምሪያ ጋር በሰራነው የተቀናጀ ስራ ካስፈተናቸው 306 ተማሪዎች ውስጥ 76.8 ከመቶ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተዋል ብለዋል።

‎መቅደስ ጌራወርቅ የፕሮግራሙን አስፈላጊነት ሲያስረዱ አካባቢው ላይ በለው ወቅታዊ ችግር  ምክንያት ትም/ቤቶች በመዘጋታቸው ተማሪዎች አቅሙና ችሎታው እያላቸው  ከትምህርት ገበታ ውጪ  እንዳይሆኑ የሚያግዝ እንደሆነ ነው። ከአሁን በፊት ፕሮግራሙ የራሱ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት በመግለጽም በያዝነው የትምህርት ዘመን አብዛኛው ችግር ይቀረፋል ብለዋል።

‎የሰሜን ሸዋ ዞን ትም/መምሪያ ኅላፊ አቶ ጸጋዬ እንግዳወርቅ የደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በማብቃት ረገድ በክልሉ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ገልጸው በዞኑ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል ብለዋል። አቶ ፀጋዬ ከባለፉት አመታት የተሻለ ውጤት የተመዘገበው በዩኒቨርሲቲው ጥረት እነደሆነም ተናግረዋል። በዘንድሮው አመት እንደ ዞን ትም/መምሪያው የተሻለ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል። ካለፈው ስህተታችን ተምረንና የነበሩ ችግሮችን ቀርፈን በዘንድሮው የትም/ዘመን በከፍተኛ ውጤት መቶ በመቶ ለማሳለፍ ነው የምንሰራው ሲሉ የዞን ትም/መምሪያ ሀላፊው የገለጹት ።

‎የሰ/ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ድጋፍና ክትትል በቅተው እንደ ሀገር ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች አሉ ብለዋል። ለዚህ ስራው የደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲና አመራሮቹ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል። የተሻሉ ተማሪዎች ላይ እና የተሻሉ መምህራን ላይ ስራውን መስራት ከተቻለ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል የዞኑ አስተዳዳሪ። ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሲማር ከርሞ ያልተፈተነ ተማሪ መኖሩን የገለጹት አቶ መካሻ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆነን ነው እየሰራን ያለነው ብለዋል። የደ/ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለመጠየቅ ዝግጁ ሆኖና ትልቅ ሀላፊነት ወስዶ ጠንክሮ በመስራቱ እንደዞን ውጤታማ መሆን ችለናል ብለዋል።

‎በአጠቃላይ በማህበረሰብ አገልግሎት የምትሰሩት ስራ የሚደነቅና የሚበረታታ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲ በያዝነው አመት ተጠናክሮና በተሻለ አደረጃጀት ፈጥሮ የሚሰራቸውን ስራዎች በዚህ መልክ አቅዶ በዛሬው የፕሮግራሙ የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ እንድንፈራረም ሲያደርግ በሰራነው ስራ ልክ እንድንጠየቅ ጭምር ነው ሲሉ የገለጹት። እስካሁን ለሰራችሁትና ወደፊትም ለምትሰሩት ስራ ሁሉ የዞኑ አስተዳደር ከልብ ያመሰግናል ያሉት አቶ መካሻ አለማየሁ ስራው ሲሰራ ችግሮች ይኖራሉ በጋራ እየገመገምን እንሄዳለን ብለዋል። 

554814950_826197273071842_1736168951082097970_n-23278.jpg 555656170_826197153071854_7765236123235101313_n-506221.jpg 554699202_826197063071863_2689943472952524965_n-669044.jpg 554695473_826197016405201_6776429124534689892_n-648607.jpg 554988316_826196986405204_3982010652641161623_n-721408.jpg 554102323_826196956405207_1020731957575212647_n-101618.jpg